Fana: At a Speed of Life!

እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ልዩ ቦታ እንዳላት ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በእስራኤል መካከል ያለው ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በእስራኤል ልዩ ቦታ አለው ሲሉ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ ገለጹ፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ በጽህፈት ቤታቸው በመገኘት አቅርበዋል፡፡

አምባሳደር ተስፋዬ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷ በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ያለውን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም ኢትዮጵያ ግድቡን ለልማት ዓላማ እየገደበች መሆኑን፣ በፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንደምታምን እና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሶስትዮሽ ድርድር ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ እንደሚያስገኝ እምነት እንዳላት ተናግረዋል፡፡

ሆኖም÷ የአረብ ሊግ በየጊዜው ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚያወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

በተጨማሪም÷ በአፍሪካ ቀንድ አከባቢ ባለው የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያን ያላትን ሚና ለፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

የእስራኤሉ ፕሬዚዳንትአይዛክ ሄርዞግ በበኩላቸው ÷ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በእስራኤል ልዩ ቦታ እንዳለው እና አምባሰደሩ በቆይታቸው ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ በእስራኤል አገር በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉላቸውም ፕሬዚዳንቱ ቃል መግባታቸውን በእስራኤል ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.