የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ አበባና ዴንቨር በጋራ የሚሰሩባቸውን ዘርፎች ወደ ተግባር መለወጥ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

By Alemayehu Geremew

May 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ እና ዴንቨር ከተሞች በጋራ የሚሰሩባቸውን ዘርፎች ወደ ተግባር መለወጥ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዴንቨር በነበራቸው ቆይታ ከከተማው ከንቲባ ማይክል ሃንኮክ ጋር በጋራ ለመሥራት የተለዩ ዘርፎችን ወደ ተግባር ለመለወጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከንቲባዋ ከከተማው አመራሮች እና የንግድ ምክር ቤት ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።

ለዴንቨር ከተማ የንግድ ምክር ቤት ኃላፊዎች እና አባላት ስለ አዲስ አበባ ሠፊ ገለፃ ማድረጋቸውን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አመላክተዋል፡፡

አዲስ አበባን ውብ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን ኃላፊዎቹ ማድነቃቸውንም ጭምር ነው ከንቲባዋ ያስታወቁት፡፡

በከተማችን አዲስ አበባ ብዛት ያለው የተማረ ወጣት እንደመኖሩ መጠን በዴንቨር ያሉ ተቋማትን በማስተባበር የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ አገልግሎቶቻቸውን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣትና ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም በተለዩ ዘርፎች ላይ በቅርበት ለመስራት በዝርዝር መወያየታቸውንም አንስተዋል።