Fana: At a Speed of Life!

በዘመናዊው የአውሮፓ እግር ኳስ የዘረኝነት ጥቃት አሁንም እልባት አላገኘም

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16 2015 (ኤፍ ) በዘመናዊው የአውሮፓ እግር ኳስ በጥቁር ተጫዋቾች ላይ የሚደርሰው የዘረኝነት ጥቃት እስካሁን አልባት አላገኘም፡፡

 በአውሮፓ እግርኳስ በተለያዩ ጊዜያት በጥቁር ተጫዋቾች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት በእግርኳስ ህግጋቶችን አልፎ ዛሬም ድረስ ይስተዋላል፡፡

 ከሰሞኑ በሪያል ማድሪዱ አጥቂ  ቪኒሺየስ ጁኒየር ከቫሌንሲያ ደጋፊዎች የደረሰበት የዘረኝነት ጥቃት እና በዕለቱ የነበሩት ዋና ዳኛ እና የቫር ዳኞች ውሳኔ  ዓለምን እያነጋገረ ይገኛል፡፡

 ቪኒ ጁኒየር ከደጋፊዎች  በደረሰበት የዘረኝነት ጥቃት ጨዋታውን አቋርጦ ለመውጣት የሞከረ ሲሆን በቡድን አጋሮቹ እና በአሰልጣኙ ካርሊቶ ምክር ጨዋታውን ቢቀጠልም የደጋፊዎቹ ትንኮሳ ግን አላቆመም፡፡

 በደጋፊዎቹ የተበሳጨው ቪኒ ጁኒየር ደጋፊዎቹን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለደረሰበት ጥቃት መልስ የሰጠ ሲሆን ፥በተፈጠረው አለመግባባት የቫሊንሲያው ተጫዋች ሁጉ ዱሮ ቪኒ ጁኒየርን ሜዳ ውስጥ አንገቱን በማነቅ ለመዳበደብ ሲሞክር ተስተውሏል፡፡

 ይሁን እንጂ የዕለቱ የቫር ዳኛ ኢግሌሲያስ ቪላኖቫ የሁጉ ዱሮን እንቅስቃሴ ምስል በመደበቅ ባንፃሩ ቪኒ ጁኒየር ትንኮሳ እንደፈፀመ በማሰመሰል ባወጣው ምስል በዕለቱ ቪኒ ጁኒየር በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

 የዓለም እግርኳስ አፍቃሪያንን ያስከፋው ይህ ክስተት ከተፈጠረ በኋላ በርካታ የእግርኳስ ደጋፊዎች በቪኒ ጁኒየር የተፈፀመውን የዘረኝነት ጥቃት እንደሚያወግዙ እና ከተጫዋቹ ጎን እንደሆኑ በማህበራዊ ገፃቸው አስተላለፈዋል፡፡

 ጉዳዩን የተመለከተው የስፔን እግርኳስ ፌዴሬሽን ማጣራት አድርጎ በዕለቱ በነበሩ ዳኞች በቫሌንሺያ ደጋፊዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስታልፏል፡፡

 በዚህም በዕለቱ የነበሩ ስድስት ዳኞች ከስራ የታገዱ ሲሆን የቫሌንሲያ እግርኳስ ክለብ 40 ሺህ ዩሮ ቅጣት እንዲከፍልና ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው አምስት  ጨዋታዎች በደቡባዊው የስታዲየም መቀመጫ ክፍል ደጋፊ እንዳይገባ ቅጣት ተላልፎበታል።

 እንደ ስካይ ሰፖርት ዘገባ ቪኒሽየስ ጁኒየር በዕለቱ የተመለከተው ቀይ ካርድ የተሰረዘለት ሲሆን ሪያልማድሪድ በቀጣይ በሚያደርገው ጨዋታ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል።

 ሳሙኤል ኤቶ፣ማሪዮ ባላቶሊ፣ዳኒ አልቬዝ ፣ሮሜሉ ሉካኩ፣ረሂም ስተርሊንግ፣ማርከስ ራሽፎርድ ፣ሙሳ ማሪጋ፣ቡካዮ ሳካ፣ ጃደን ሳንቾ እና ሌሎችም ጥቁር ተጫዋቾች በዘመናዊው የአውሮፓ እግር ኳስ የዘረኝነት ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.