የሀገር ውስጥ ዜና

ንግድ ባንክ በ“ዲጂታል ባንኪንግ” የ2 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር ግብይት መፈጸሙን አስታወቀ

By Alemayehu Geremew

May 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ“ዲጂታል ባንኪንግ” አገልግሎት የ2 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር ግብይት መፈጸሙን አስታወቀ፡፡

በተዘረጋው ሥርዓት የገንዘብ ዝውውሩ የተካሄደው ባለፉት ዘጠኝ ወራት መሆኑንም የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወረቀት የፀዳ አገልግሎትና ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን በማንሳት ኢትዮጵያም ሥርዓቱን እየተቀላቀለች መሆኗን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዲጂታል ግብይት የገንዘብ ዝውውርን በቀላሉ ለመመዝገብ፣ ለማስተዳደር ፣ መልሶ ለማየትና ለማረጋገጥ እንዲሁም መረጃ አሰባስቦ ለመተንተንና ውሳኔ ለመስጠት አመቺ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ባንኩ የሞባይል ባንኪንግ፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ ፣ የሞባይል ዋሌት ፣ የኤቲ ኤም ፣ የፖስ ማሽንና ሌሎች የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ወደ ተግባር በማስገባት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን እያገዘ ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ሐብት 1 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር መድረሱም ተገልጿል፡፡