ለ16 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የርክበ ካሕናት ምልዓተ ጉባዔ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ16 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የርክበ ካሕናት ምልዓተ ጉባዔ በዛሬው እለት ተጠናቋል።
የጉባዔውን መጠናቀቅ አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ÷ ምልዓተ ጉባዔው ለቤተክርስቲያኗ አንድነት፣ ሀዋሪያዊ ተልዕኮ እና መንፈሳዊ እድገት እንዲሁም ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በብፁዓን ሊቃነጳጳሳት የሚመራ፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ተቋማት ጋር የሚሰራ በመንግስትም ሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የሚኖረው የሰላም ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሰይሟልም ነው ያሉት፡፡
በኦሮሚያ በሚገኙ አህጉረ ስብከት ተፈጥሮ የነበረው ወቅታዊ ችግር እንዲቀረፍ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን በመሰየም ከፌደራልና ኦሮሚያ ክልል ጋር በመወያየት ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶሱ መወሰኑንም ተናግረዋል።
በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች አህጉረ ስብከቶች ላይ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙንም ነው የገለጹት፡፡
በትግራይ አህጉረ ስብከት ተቋርጦ የነበረው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ግንኙነት እንዲቀጥል ቀደም ሲል የተሰየመው ልዑክ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል መወሰኑንም ነው የተናገሩት።
በቅድስት አባተ