Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ፑቲን ለአፍሪካ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ለአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና መንግስታት እንዲሁም ህዝቦች “ለአፍሪካ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበት 60ኛ ዓመት በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

ፑቲንም የምስረታውን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም አፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን ያሸነፉበት የነፃነት ፣የሰላምና የብልፅግና ምኞቶችን ያቀፈ ድል ማሳያ ለሆነው የአፍሪካ ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

የአፍሪካ መንግስታት በጋራ ባደረጉት ጥረት ለአካባቢያዊ ቀውሶች የጋራ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘዴዎችን እና የቀጣናዊ ውህደት ሂደትን ማስጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ለአህጉሪቱ ማህበበረ -ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና አፍሪካ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ነው ያነሱት።

ፑቲን በመልዕክታቸው ሩሲያ ከአፍሪካ አጋሮች ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር ሁልጊዜ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በፈረንጆቹ 2019 ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የሩሲያ – አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤም ሩሲያ ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከሩን ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው የሩሲያ – አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በመጭው ሐምሌ ወር በሴንት ፒተርስበርግ እንደሚካሄድ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፥ ጉባኤው ሩሲያ ከአፍሪካ አጋሮች ጋር በፖለቲካ፣ ንግድ እና ኢኮኖሚ፣ ሳይንሳዊ እና ቴክኒካል፣ ሰብአዊ ድጋፍን ጨምሮ በሌሎችም አዳዲስ ዘርፎች ያላትን ትብብር ለማሳደግ እንደሚያግዛትም ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.