ዓለምአቀፋዊ ዜና

በምሥራቅ አፍሪካ ተጎጂዎችን ለመደገፍ የሚውል 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መገኘቱ ተነገረ

By Alemayehu Geremew

May 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምሥራቅ አፍሪካ የሚያደርገውን እርዳታ ለመደገፍ የሚውል 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር አገኘ።

የተገኘው ገንዘብ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ እና ሶማሊያ ለሚገኙ ወደ 32 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሚውል መሆኑ ታውቋል።

ድጋፉ የተመድ አጋር ከሆኑ ማኅበረሰቦች ፣ ሰብዓዊ ድርጅቶች ፣ ባለሥልጣናት እና ለጋሾች መገኘቱን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) መረጃ ያመላክታል፡፡

ዛሬ ቃል የተገባውን የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የተቻለው በኒውዮርክ በተዘጋጀ ከፍተኛ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር ላይ ሲሆን ተመድ በምስራቅ አፍሪካ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመርዳት 7 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልጾ ነበር፡፡

መርሐ-ግብሩን ተመድ ፣ ጣሊያን፣ ኳታር ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ከኢትዮጵያ ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ መንግስታት ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን እና ኔዘርላንድስ አብዛኛውን ገንዘብ ለመስጠት ቃል የገቡ ሀገራት ናቸው።

በቀጣናው ባለፉት 5 የዝናብ ወቅቶች በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ በተከሰተው ድርቅ፣ በግጭት ለተጎዱ እንዲሁም የሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተረጋጋ ባለመሆኑ ድጋፉ ማስፈለጉም ነው የተገለጸው፡፡

የተገኘው ድጋፍ ተጎጂዎችን በጊዜያዊነት ለመደገፍ እንጂ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ እንዳልሆነ ተጠቁሟል፡፡