ምክር ቤቱ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትበ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ22ኛ መደበኛ ስብሰባው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
የራስገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጣቸው ተቋማዊና አስተዳደራዊ ነጻነት በመጠቀም በመማር ማስተማር እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራዎች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት የሚያከናውኑ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላትም ጥያቄዎችና አስተያየቶች በስፋት መቅረባቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አነስተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍለው መማር ስለማይችሉ ከሌሎች እኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙ ሊያደርግ ስለሚችል አዋጁ ጊዜውን የጠበቀ አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም በስፋት ተነስተዋል፡፡
በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ፥ አዋጁ በሀገሪቱ የተጀመረውን የትምህርት ጥራት ሪፎርም የሚያጠናክር መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ከተለመደው የቢሮክራሲ አሰራር በመውጣት ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲሰሩ የሚያስችላቸው አዋጅ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ ፥ አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጡና የሚጠኑት ጥናቶችም ችግር ፈቺ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎች ጫና እንዳይኖርባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን ጠቁመው ፥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ወደ ራስ ገዝነት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲያጎለብቱ የሚያስችል መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በ4ተቃውሞ እና በ13 ድምጸ ተአቅቦ አዋጅ ቁጥር 1294/2015 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡