በኦሮሚያ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ4 ቢሊየን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል – የክልሉ ግብርና ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮው ዓመት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ4 ቢሊየን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኤሊያስ ከድር÷ ለዘንድሮው ዓመት አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በክልሉ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው በዋናነት ለፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት በመስጠት የችግኝ ማፍላት ስራ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።
ለችግኝ ተከላ የሚሆን ቦታ መረጣና ጉድጓድ ዝግጅትም ቀደም ብሎ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በክልል ደረጃ ከሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ እንደሚካሄድ የጠቀሱት ሃላፊው ለዚህም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን በበጎ ፈቃድ ለማሳተፍ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ 13 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፤ የጽድቀት መጠናቸውንም 88 ነጥብ 6 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአገር ዓቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ዝግጅት በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማሳወቃቸው ይታወሳል።