በኦሮሚያ እና አማራ ክልል የበረሃ አንበጣ መንጋ በበልግ ምርት ላይ የደቀነውን ስጋት ለመቀነስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የበረሃ አንበጣ መንጋ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች መከሰቱን ተከትሎ የበልግ ምርት ላይ የደቀነውን ስጋት ለመቀነስ ስራ ተጀምሯል።
በኦሮሚያ ክልል በተለይም በባሌ እና ቦረና ቆላማ አካባቢዎች አንበጣው በመከሰቱ የበልግ ምርት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በባህላዊ እና በዘመናዊ ዘዴዎች የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ገልጸዋል።
በክልሉ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች 8 ቦታዎች ላይ ለዚሁ ስራ የተቋቋመው ግብረ ሀይል ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአማራ ክልልም መንጋው በ38 ወረዳዎች በ33 ሺህ 742 ሄክታር መሬት ላይ መከሰቱን እና የመከላከል ስራም እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ተናግረዋል።
በሰሜን እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ሰሜን ጎንደር ዞኖች የበረሀ አንበጣው መከሰቱን የተናገሩት ዶክተር መለስ መኮንን የመከላከል ስራው ላይ ትኩረት ተደርጓልም ብለዋል።
የበረሃ አንበጣ መንጋውን ከመከላከል ጎን ለጎን አርሶ አደሩ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሁለቱም ክልሎች በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊዎቹ አስረድተዋል።
በሁለቱም ክልሎች አርሶ አደሩ የኮሮና ቫይረስን በመከላከል የግብርና ስራውን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያከናውን እና ከዚህ ቀደም በበለጠ መልኩ ምርታማነት ላይ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን የስራ ሀላፊዎቹ አስታውቀዋል።
በዙፋን ካሳሁን
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።