Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብስባ በግብጽ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብስባ በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ስብሰባው ከአመታዊው የአፍሪካ ልማት ባንክ ጉባኤ ጎን ለጎን እየተካሄደ ሲሆን፥ በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ ለቀጣናዊ ውህደት ምክትል ፕሬዚዳንት አኪን ኦሉግባዴ መመራቱን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በስብሰባው የልማት አጋር የሆኑት የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም ባንክ እና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፥ ዋና ትኩረቱንም የግሉ ዘርፍ በአፍሪካ ቀንድ በሚኖረው ሚና ላይ አድርጓል።

ሚኒስትሮቹ በመድረኩ በቀጠናው ለሚተገበሩና በተለይም አረንጓዴ እና ዘላቂ ልማትን ለሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ባለሃብቶችን ለመሳብ ከግሉ ዘርፍ ጋር መስራት ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ መክረዋል።

በቀጠናው ባሉ ኢንቨስትመንትና በሚተገበሩ ፕሮጄክቶች ላይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ የሚኖረውን ሚና በተመለከተም ተወያይተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የግሉ ዘርፍ በቀጠናው ለሚያከናውነው ኢንቨስትመንት አስቻይና ምቹ ከባቢ መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ይህን ማድረጉም ለኢኮኖሚያዊ እድገት ብቻ ሳይሆን ለአካባቢያዊ ሰላምና ደህንነት አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ በአፍሪካ ቀንድ የድንበር አካባቢዎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገትና ልማት ለማሳደግ ያግዛል በተባለው ስትራቴጂክ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.