Fana: At a Speed of Life!

ለፕራይም ቴሌቪዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ለፕራይም ቴሌቪዥን ጣቢያ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡

ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ፥ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መገናኛ ብዙኃን በዜጎች መካከል አብሮነትን ከሚሸረሽር እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለአለመተማመን ከሚዳርግ የይዘት ስርጭት እንዲቆጠቡ ግዴታ ይጥላል ብሏል፡፡

አክሎም ፥ በኢፌዴሪ ህገመንግስት፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እና በሌሎች ተያያዥ ሕጎችም የመገናኛ ብዙኃን በተለይም የጋራ እሴቶችን የሚንዱ፣ አለመቻቻል እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ እና ዜጎችን ለግጭት ሊያነሳሱ የሚችሉ ስርጭቶችን ከማስተላለፍ እንዲታቀቡ ይደነግጋሉ፡፡

በዚህም ፕራይም ቴሌቪዥን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ሕግጋት የሚጥሱ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን ሲያሰራጭ መቆየቱን በክትትል ሥራችን አረጋግጠናል ያለው ባለስልጣኑ ፥ ከክትትል ውጤቱም በመነሳት በተደጋጋሚ እርምት እንዲወሰድ ግብረመልስ ተሰጥቶታልም ነው የተባለው፡፡

ግንቦት 4 ቀን 2015ዓ.ም በባለሥልጣኑ ጽህፈት ቤት ውይይት ማካሄዳችን ይታወቃል ነው ያለው ባለስልጣኑ፡፡

ይሁን እንጂ ፕራይም ቴሌቪዥን ስህተቱን በመቀጠል የዜጎችን አብሮነት የሚጎዳ፣ ይልቁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚሹ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አሉታዊና ሕግን የሚተላለፉ ይዘቶችን በማሰራጨት ዜጎችን ላልተገባ ውጥረትና አደጋ አስተዋፅኦ የማድረግ አዝማሚያ እንደታየበትም ተጠቁሟል፡፡

ይህም በተለይም ፕራይም ቴሌቪዥን እንደ ንግድ ብሮድካስተር ከገባው የውል ግዴታና ከተቋቋመለት ዓላማ አንጻር ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል ሲልም ባለስልጣኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በዚህም ም ፕራይም ቴሌቪዥን ከዚህ ድርጊቱ እንዲታረም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑን አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.