የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የ765 አቅመ ደካሞችን ቤት አደሰ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ባለፉት ዘጠኝ ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የ765 አቅመ ደካሞችን ቤት ማደሱን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሐፊ ይሁነኝ መሐመድ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሰሩ ስራዎችና በቀጣይ የክረምትና የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የማህበሩ አባላት የሆኑ በርካታ ወጣቶች በመተጋገዝ ባለፋት ዘጠኝ ወራት በበጋና በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የ765 የአቅመ ደካሞች ቤት በሙሉና በከፊል ማደሳቸውን ተናግሯል።
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከቤት ማደሱ በተጨማሪ በትራፊክ ማስተናበር፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ለህክምና የሚመጡ ዜጎችን በማስታመም፣ በማዕድ ማጋራትና በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ መሳተፋቸውንም ጠቅሷል።
በተለይም የቤት ዕድሳቱ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት፣ ከማህበሩ ወጪ፣ ከአባላት በተሰበሰበ ገንዘብና በማህበረሰቡ ድጋፍ መከናወኑን ገልጿል።
ይህንኑ ተግባር በቀጣይም ከሰኔ 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ በጀት አመቱ መጠናቀቂያ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ለማስቀጠል የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁሟል።
ማንኛውም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅትን ታሳቢ ማድረግ እንደሌለበት ገልጾ፥ አቅም ያለውና ኃላፊነት የሚሰማው ሁሉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል።
ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠታቸው በተጨማሪ የአካባቢያቸውን ሰላም በማስከበር ረገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግሯል።