ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን በማፍለቅ ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ በትኩረት ይሰራል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የወጣቶችን ክህሎትና ተወዳዳሪነት በማጎልበት ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን በማፍለቅ ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ በትኩረት እንደሚሰራ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
“ክህሎት ለተወዳዳሪነት” በሚል መሪ ሀሳብ ላለፋት አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር የመዝጊያ መርሐግብር ተካሂዷል።
በመዝጊያ መርሐ-ግብሩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተካሄደው የውድድር መድረክ 267 የሚሆኑ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች በተለያዩ ዘርፎች የክህሎት ውድድር ማካሄዳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በውድድሩ መዝጊያ መርሐ-ግብር ላይ በ18 የተለያዩ ዘርፎች አሸናፊ የሆኑ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በዚህ መሰረት ውድድሩን በአንደኛ ደረጃ ላጠናቀቁ የ100 ሺህ ብር ፣ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቷል።
ውድድሩን በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቁ ደግሞ የ80 ሺህ ብር የገንዘብ እና የብር ሜዳሊያ የተሸለሙ ሲሆን፥ በተመሳሳይ የእውቅና ሰርቲፊኬት አግኝተዋል።
በውድድሩ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው የጠናቀቁ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ደግሞ የ60 ሺህ ብር ሽልማትና የነሀስ ሜዳሊያ ከሰርተፊኬት ጋር ተቀብለዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት እና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች የተዋወቁበት መሆኑንና አዳዲስ እሴት የታከለባቸው የቴክኖሎጂ ግኝቶች የተገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በግብርና፣ ማዕድን፣ማምረቻ፣ቱሪዝም እና በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የወጣቶችን ክህሎትንና ተወዳዳሪነት በማጎልበት ችግር ፈቺ ፈጠራዎች ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ ይሰራል ብለዋል።
በውድድሩ የቀረቡ ቴክኖሎጂዎች በተጨባጭ ኢኮኖሚው ላይ እሴት የሚጨምሩ እና ከተቀመጠው የልማት አቅጣጫ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ3ኛውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር መድረክ በይፋ በከፈቱበት ወቅት ኢትዮጵያን ለመለወጥ መፍትሄ ተኮር ፈጠራዎችን ማብዛት እንደሚገባ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡