የሀገር ውስጥ ዜና

የህወሓት ታጣቂ ሃይሎች የመጀመሪያው ዙር የተሃድሶና መልሶ የማቋቋም መርሐ ግብር ተጀመረ

By Amele Demsew

May 26, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት ታጣቂ ሃይሎች የመጀመሪያው ዙር የተሃድሶና መልሶ የማቋቋም መርሐ ግብር ዛሬ ከመቀሌ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ኩሐ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያ እንደገለጹት÷ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።

“ታጣቂዎች በዚህ ሰላም ተጠቅማችሁ የራሳችሁን ህይወት መቀየርና፥ በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ ልማት መሳተፍ፤ የተፈጠረውን ሰላምም ዘላቂ ለማድረግ መስራት ይኖርባችኋል” ብለዋል።

መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ወደ መደበኛ ህይወታችሁ እስክትመለሱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ ለተሀድሶ የገቡት እስከሚቋቋሙ ድረስ ተገቢው ዕገዛ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

የህወሓት ታጣቂ ሀይሎች ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሀይለ በበኩላቸው፥ “እናንተ የተሀድሶ መርሐ ግብርን አጠናቃችሁ ወደ ህብረተሰቡ ስትመለሱ የልማትና የሰላም ሀይል መሆን አለባችሁ” ብለዋል።

በመጀመሪያው ዙር የህወሓት ታጣቂ ሀይሎች ተሀድሶ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ስምምነቱ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ማረጋገጥ ኮሚቴ አባላት መገኘታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ዛሬ የተጀመረው መርሐ ግብር የመጀመሪያ ዙር መሆኑ ተገልጾ በተመረጡ 10 ቦታዎች በተመሳሳይ የተሀድሶ መርሐ ግብሩ እንደሚካሄድ ተገልጿል።