የሀገር ውስጥ ዜና

የማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጊዜያዊ  እግድ ተነሳ

By Shambel Mihret

May 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጊዜያዊ እግድ መነሳቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የተሰጠውን ጊዜያዊ ዕግድ አስመልክቶ በደብዳቤ መጠየቁን ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም በቴሌቪዥን ጣቢያው የተላለፈው ዘገባ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት የሚታይ መሆኑን ገልፆ÷ የቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ የተሰጠው ጊዜያዊ ዕግድ እንዲነሳ ጠይቋል ብሏል፡፡

የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ሃይማኖታዊ አስተምሮ እና በጎ ዕሴቶችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ እንዲሁም በሚያስተምሯቸው ዕሴቶች ሕግና አሠራርን አክብረው በማስከበር እና ለሀገር ሠላም እና አንድነት አበክረው በመስራት ረገድ አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ይታመናልም ነው ያለው ባለስልጣኑ፡፡

በአንፃሩም በሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የሚሠራጩ አሉታዊ ሚና ያላቸው ይዘቶች ከሚያስከትሉት አሉታዊ ውጤት አንፃር በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊመሩ እንደሚገባም ገልጿል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት በቀጣይ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግ እምነት እንዳለው ጠቅሶ÷የቴሌቪዥን ጣቢያውም የሚያሠራጫቸውን ሥርጭቶች በጥንቃቄ እንዲያሠራጭ አሳስቧል፡፡

ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም የተሰጠው ጊዜያዊ  ዕግድ ከግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተነሳ መሆኑንም ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አሳውቋል፡፡