Fana: At a Speed of Life!

በ12 የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በ12 የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቀደ፡፡

 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በ4 መዝገብ የቀረቡ 28 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል።

 

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ መዝገቦች ካቀረባቸው 28 ተጠርጣሪዎች መካከል መስከረም አበራ፣ ሳሮን ቀባው፣ ቢሰጥ ተረፈ፣ዳዊት በጋሻሁ፣ቴድሮስ አስፋው፣ መንበረ አለሙ ፣ ሲሳይ መልካሙ ፣ ገብርዓብ አለሙ (ዶ/ር)፣ ዳዊት እባቡ፣ቴድሮስ ተሾመ፣ አንደበት ተሻገር እና ማስረሻ እንየው ላይ የምርመራ ስራውን ማጠናቀቁንና መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን አስታውቋል።

 

የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በፖሊስ ሲከናወን የቆየውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።

 

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ተጠርጣሪዎች በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ምርመራ ሲከናወንባቸው በቆዩባቸው ጊዜያት  ምርመራውን ሲመራ እንደነበር ጠቅሰው÷እንደ አዲስ ክስ ለመመስረት 15 ቀን ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢ አይደለም ሲሉም ተከራክረዋል።

 

የመመስረቻ ጊዜ የሚሰጥ ከሆነ ደግሞ የዋስትና መብታቸው ይፈቀድ ሲሉም  ጠይቀዋል።

 

መስከረም አበራን በሚመለከት በሙያዋ የፖለቲካ ተንታኝ ሆና በሰጠችው ትንታኔ  ምክንያት መታሰር አይገባትም በማለት የተጠረጠረችበት ጉዳይ በቀጥታ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ድንጋጌ መሰረት ነው መታየት የሚገባው ሲሉ ተከራክረዋል።

 

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ መስከረም አበራን በተመለከተ ከሚዲያ ሙያ ውጪ ባላት ተሳትፎና በተገኘ ማስረጃ ምክንያት ተጠርጥራ መያዟን በመግለጽ  መልስ የሰጠ ሲሆን÷  ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር  ማንንም ይዘን አላቀረብንም በማለት አስረድቷል።

 

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ÷ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዓቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

 

በሌላ በኩል በ4 መዝገቦች ተነጣጥለው የቀረቡ 11 ተጠርጣሪዎች በቀለ ኃይሌ(ዶ/ር) ፣ጌታቸው ጡም ልሳን፣ሀብታሙ ዳኘው፣ ሙሉቀን ወንዴ፣ ጌታወይ አለሙ፣ጌታነህ ወንደሰን፣ ጌታቸው ወርቄ፣ታደሰ አዳነ  ዮርዳኖስ አለሙ፣ተስፋዬ መኩሪያው፣ ወንደሰን ተገኝን በሚመለከት መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ  ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጾ ለቀሪ የምርመራ ስራ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

 

በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በኩል÷ ከዚህ በፊት በሌላ ፍርድ ቤት በሁከትና ብጥብጥ ወንጀል ተጠርጥረው ሲቀርቡ የተሰራ እንጂ አሁን በተሰጠው የተሰራ አደለም ሲሉ በመቃወም ተጨማሪ ጊዜ መሰጠት እንደሌለበት ገልፀው ተከራክረዋል።

 

መርማሪ ፖሊስ  በተሰጠው ጊዜ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ገልጾ÷ ፍርድ ቤቱ ከምርመራ መዝገቡ ላይ የሰራቸውን ስራዎችን መመልከት ይችላል ሲል መልስ ሰጥቷል።

 

የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ላይ የተነሱ አጠቃላይ ክርክሮችን የመረመረው ችሎቱ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ  ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ አስፈላጊነት መታመኑን በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ የ10 ቀን ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።

 

በተለያዩ መዝገቦች ምርመራ ሲደረግባቸው የነበሩት  አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)፣ታደለ መንግስቱ፣ትዛዙ ታረቀኝ፣ ምስጋናው ማሩና ሰይፈ ተስፋዬን የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት   ከ10 ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ ዋስትና አሲዘው ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዷል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.