Fana: At a Speed of Life!

ከጁምዓ ሶላት በኋላ በመርካቶ አካባቢ በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሰው ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች መስጂዶች ፈርሰዋል በሚል ምክንያት በመርካቶ ዙሪያ በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

 

ፖሊስ ባወጣው መግለጫ በተፈጠረው ረብሻና ግርግር ህግ በማስከበር መደበኛ ሥራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱንም አስታውቋል።

 

በተለይም በተለምዶ ጋዝ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተፈጥሮ በነበረ ግርግር ሁለት ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ሆስፒታል ከተላኩ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉንም ነው የገለጸው።

 

በተጨማሪም አራት ግለሰቦች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ህግን ለማስከበር በተሰማሩ 37 የፖሊስ አመራርና አባላት እንዲሁም 15 የሚሆኑ የተለያዩ የፖሊስ አጋዥ ሀይሎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና መላካቸውንም ገልጿል።

 

ረብሻውን ባስነሱት አካላት በተጨማሪ ንብረትነታቸው የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በሆኑ ሁለት አውቶቡሶች ላይ ጉዳት መድረሱንም በመግለጫው አመላክቷል።

 

መነሻውን አንዋር መስጂድ ያደረገው ረብሻ በጋዝ ተራ፣ ቆርቆሮ ተራ፣ ሰባተኛ አካባቢ፣ አመዴ እና በተለያዩ አካባቢ ለማዛመት የተሞከረ ቢሆንም በፀጥታ አካሉ ጥረት ረብሻው ሳይስፋፋ መቆጣጠር ተችሏልም ነው ያለው።

 

በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ ረብሻ እንደተነሳ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው መረጃ የተጋነነ ከመሆኑም ባሻገር አጋጥሞ የነበረው ብጥብጥ በቁጥጥር ስር ውሎ አካባቢው ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ መግባቱን የገለጸው ፖሊስ፥ ብጥብጡን በመምራትና በማስተባበር እንዲሁም ዋነኛ ተሳትፎ የነበራቸው 114 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ በህግ አግባብ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ነው ያስታወቀው።

 

ፖሊስ በመግለጫው በአዲስ አበባ ከተማ በህዝበ ሙስሊሙም ሆነ በዕምነት ተቋሙ ላይ የተፈጠረ ችግር ሳይኖር በሌሎች ቦታዎች ላይ መስጂድ ፈርሷል በሚል ምክንያት ህገ-ወጥ ሰልፍ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡

 

በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አቅደው በተንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ የፀጥታ አካላት እየወሰዱት ያለውን እርምጃ አጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን፥ የከተማችንን ሠላምና ፀጥታ ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.