Fana: At a Speed of Life!

ዘመን ባንክ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ባለ 36 ወለል ህንጻ አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘመን ባንክ በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው ባለ 36 ወለል የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

 

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ  የብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ  እና የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ እሸቱን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

 

አቶ ኤርሚያስ እሸቱ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ÷ዘመን ባንክ በ15 አመታት ስኬታማ ጉዞው የአገልግሎት አድማሱን በማስፋትና የማዕከላቱን ቁጥር በመጨመር ተደራሽነቱን እያሰፋ ይገኛል፡፡

 

ከጊዜው ጋር የሚዘምኑ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ለደንበኞች ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

 

ዘመን ባንክ በ2021/22 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ አትርፏል ያሉት አቶ ኤርሚያስ፥ ጠቅላላ ሃብቱም 40 ቢሊየን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡

 

ባንኩ ዛሬ ያስመረቀው ባለ 36 ወለል ህንጻ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ጠቁመው ÷ ለባንኩ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ለከተማዋ ልዩ ውበት የሚያጎናጽፍ ከመሆኑ ባሻገር ባንኩ የደረሰበትን ከፍታ የሚገልጽ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

በ2 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈው ህንጻው÷ የስብሰባ አዳራሾች፣ የአካል ብቃት ማጎልበቻ ክፍሎች፣ 6 አሳንሰሮች፣ 200 መኪና የሚይዙ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችና ሌሎች ክፍሎች አሉት ተብሏል፡፡

 

ዘመን ባንክ ከ15 ዓመታት በፊት በ87 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን፥ አሁን ላይ በ100 ቅርንጫፎች 35 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

 

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.