የፌደራል እና ክልል ፍርድ ቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ በመቀሌ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ መቀሌ ተካሂዷል።
በመድረኩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረትን ጨምሮ ሁሉም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና የሥራ ኃላፊዎች ፣ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የሁሉም ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በጦርነቱ ወቅት በክልሉ ተቋርጦ የነበረው የፍርድ ቤት የተሟላ የዳኝነት አገልግሎት እንዲቀጥል ለማገዝ በማሰብ መድረኩ በመቀሌ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የሕግ የበላይነትን በማስፈን ውስጥ ፍርድ ቤቶች የሚጠበቅባቸውን የማይተካ ተቋማዊና ሕገመንግስታዊ ሚና መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉም አካላት መገንዘብና ለሕግ የበላይነትና ሰላም መስፈን አዎንታዊ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መረጃ ያመላክታል።
በጦርነቱ ምክንያት የዳኝነት ሥራቸውን ያቆሙና የወደሙ የትግራይ ክልል ፍርድ ቤቶች በዘላቂነት መደገፍ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሦስቱን የፌደራል ፍርድ ቤቶች በማስተባበር ለትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሥራ ማስጀመሪያ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ቋሚ እና አላቂ የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋይ ገብረመድህን በበኩላቸው፥ የምክክር መድረኩ በመቀሌ መከናወኑ ለዳኝነት ነፃነትና ለሕግ የበላይነት እንዲሁም ፍርድ ቤቶች የተጣለባቸውን ሕገመንግስታዊ ኃላፊነት በመወጣት የተሟላ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ክልሉን ለመደገፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።
የትግራይ ክልል ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ የፍርድ ቤቶች ሚና የጎላ መሆኑን በማንሳት ፍርድ ቤቱ እያከናወነ ያለውን ተቋማዊ ፣ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ሥራ የብዙ አካላት ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ “በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ክልል ፍ/ቤቶች የተፈጠሩ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫ” እንዲሁም “የፌደራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች የጣምራነት ሥልጣን እና የትብበር ሥራ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።