Fana: At a Speed of Life!

በፍትሕ  ዘርፍ  ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት-አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍትሕ ዘርፉ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የፍትሕ ሚኒስቴር በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር የፍትሕ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ላይ ከፌደራልና ክልሎች የፍትሕ ተቋማት ኃላፊዎችና የክልል ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎች ጋር ተወያይቷል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ በፍትሕ ዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና በጎ ጎኖችን ለማጽናት ያለመ ነው።

በትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ በፍትሕ ዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላሉ ተብለው የተለዩ 10 የተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮግራሙን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የፍኖተ-ካርታ ዝግጅት እንዲሁም የድርጊት መርሐ ግብር መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በፍትሕ ዘርፉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በዘርፉ ያሉ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ማጠናከር አለባቸውም  ነው ያሉት።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው÷መንግሥት ይህንን ፕሮግራም ለመፈጸም ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ ከኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው÷ለተግባራዊነቱ ርብርብ መደረግ አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.