Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
 
አቶ ደመቀ÷ በቻይና የኢንቨስትመንት ዋና ማዕከል በሆነችው ጉዋንግዡ በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተሳትፋዋል፡፡
 
በመድረኩ ከሶስት መቶ የሚበልጡ በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ማዕድን፣ ሃይል፣ ፋርማሲዩቲካልና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ታዋቂ ባለሃብቶች መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡
 
አቶ ደመቀ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ጠቅሰው ÷ ይህም በኢኮኖሚው መስክ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል፡፡
 
የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
የጓንዶንግ ግዛት የንግድ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዣዎ ቺን በበኩላቸው÷ በጓንዶንግ በማኑፋክቸሪንግ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በማዕድን፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና ሌሎችም ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በርካታ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገብተው መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
 
በቻይና የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው ÷ የኢኮኖሚ መድረኩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
 
አቶ ደመቀ ከተለያዩ ከፍተኛ አቅም ካላቸው ኩባንያዎች ኃላፊዎችና መስራቾች ጋር ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
 
በውይይታቸውም ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ መጋበዛቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.