Fana: At a Speed of Life!

የቱርክ ሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሒደት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ ሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣት ሒደት ተጠናቅቋል፡፡

በፈረንጆቹ ባሳለፍነው ግንቦት 14 ቀን በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተፎካካሪዎች አብላጫ ድምፅ ባለማግኘታቸው ወደ 2ኛ ዙር ድምጽ የመስጠት ሂደት መሸጋገሩ ይታወሳል፡፡

በመጀመርያው ዙር ምርጫ የፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ሕዝባዊ ህብረት ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን በ49 ነጥብ 52 በመቶ አብላጫ ድምፅ መርቶ ነበር፡፡

የእርሳቸው ዋነኛ ተቀናቃኝ ሆነው የቀረቡት ኪሊዳሮግሉ ደግሞ በጠባብ የድምፅ ልዩነት 44 ነጥብ 99 በመቶ የሚሆነውን የ መራጮች ድምፅ አግኝተው እንደነበር ይታወቃል፡፡

በሁለተኛው ዙር ምርጫም ኤርዶኻን ከዋናው ተቃዋሚ ሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ ሊቀመንበር እና ከስድስት ፓርቲዎች ጥምረት ኔሽን አሊያንስ የጋራ እጩ ከማል ኪሊዳሮግሉ ጋር ተፋጠዋል።

በአሁኑ ምርጫ የመጀመሪያው ዙር 4 ነጥብ 9 ሚሊየን መራጮችን ጨምሮ ከ60 ሚሊየን በላይ መራጮች መመዝገባቸው ተመላክቷል፡፡

ለምርጫው በሀገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ 191 ሺህ 885 ድምጽ መስጫ ሳጥኖች አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ቲ አር ቲ በዘገባው አስፍሯል፡፡

የአካባቢ ምርጫ አስፈፃሚዎች በህመም እና በአካል ጉዳት ምክንያት ድምጽ መስጠት ላልቻሉ ዜጎች ተንቀሳቃሽ ድምጽ መስጫ ሳጥኖችን መኖሪያ ቤታቸው ድረስ መውሰዳቸው ተነግሯል።

አሁን ላይ የድምጽ ቆጠራ ሒደቱ በሁለም የምርጫ ጣቢያዎች መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.