Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብና ባለሃብቶች የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብና ባለሃብቶች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል።
“ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ” በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽን ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ለተመልካቾች ክፍት መደረጉ ይታወቃል።
በአውደ ርዕዩ ላይ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ የተለያዩ ስኬቶችን የሚያሳዩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች፣ ዲጂታላይዜሽንና የግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
በዚህም የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ በተለያዩ የክፍል ደረጃ ያሉ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም አውደ ርዕዩን ጎብኝተዋል።
በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብና ባለሃብቶች በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ ታዳሚዎች መካከል የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጀነር መላኩ አዘዘው÷በጉብኝቱ በርካታ አስደናቂ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን ተመልክተናል ብለዋል።
በግብርናው የተገኙ ስኬቶችና የፈጠራ ስራዎች በቀጣይ ለዘርፉ እድገት ትልቅ ተስፋ የሰነቁ በመሆናቸው ጥሩ ጅምር አለ ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች በአውደ ርዕዩ በተመለከቷቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደተደነቁ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያ ግብርና ያለፈበትን ሂደትና አሁን የደረሰበት ደረጃ የንግዱ ማህበረሰብና ባለሃብቶች ማየታቸው የላቀ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርናን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የባለሃብቱና የንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
በቀጣይ በተመረጡ የግብርና መስኮች ለመሠማራት ለሚሹ ባለሃብቶች አውደ ርዕዩን መጎኘብት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ዶክተር ሶፊያ ገልጸዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.