ለሸገር ዳቦ ፋብሪካ በኦን ላይን ስልጠና ብቁ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅርቡ ስራውን ለሚጀምረው ለሸገር ዳቦ ፋብሪካ በኦን ላይን ስልጠና ብቁ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉን ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከካቢኔ አባላት ጋር በመሆን የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታ ያለበትን ደረጃ መመልከታቸውን አስታውቅዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ጋር በታሰበው ወቅት ለማስመጣት ፈታኝ ሁኔታዎች ቢገጥሙንም የማሽን ተከላው በሚያስገርም ፍጥነት እየተጠናቀቀ መሆኑን መታዘባቸውንም በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ ገልፀዋል።
ለምርት የሚሆን የግብዓት ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ የተወሰኑ ማሽኖች ወደሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ፋብሪካው ወደስራ የሚገባ ይሆናልም ብለዋል።
ስራውን የሚያስጀምሩና ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ስልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎች ወደሀገር ውስጥ መምጣት ባይችሉም “በኦን ላይን ” ስልጠና በመስጠት ብቁ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ማፍራት እንደተቻለም አክለው ገልፀዋል።
“በኢትዮጵያ የመገንባት አቅም 3 ዓመታት ይወስድ የነበረ ፋብሪካ በወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ጫፍ ላይ በመድረሳችንና በሂደቱም ብቁ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በማፍራታችን ኩራት ተሰምቶኛል” ብለዋል ኢንጂነር ታከለ ኡማ።
በተያያዘ ዜና ለረጅም ዓመታት በብልሽት ቆመው የነበሩ ከ400 በላይ አንበሳ የከተማ አውቶቡሶች በሚመች አኳኋን እድሳት ተደርጎላቸው ለሸገር ዳቦ መሸጫና ማከፋፈያነት ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል።
በከተማዋ ያለውን የመስሪያና መሸጫ ቦታ ችግር ከመፍታት አኳያ አውቶቡሶቹ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸውም ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሃላፊዎች ገልጸዋል።
የጥገና አገልግሎቱ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ በዋነኝነት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች በየአቅራቢያቸው የዳቦ አቅርቦት እንዲያገኙ የሚያደርግ ሆኗል።
ሸገር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ወደ ሥራ ሲገባ በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት ሲሆን ምርቱም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለ የማኅበረሰብ ክፍልን ባገናዘበ ዋጋ የሚያከፋፍል ይሆናል።