ተሽከርካሪ አምራቾች በየአመቱ 74 ሚሊየን ቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ያመነጫሉ – ግሪን ፒስ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ትላልቅ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች በየአመቱ 74 ሚሊየን ቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ እንደሚያመነጩ ዓለም አቀፉ የአካባቢ መብት ጥበቃ ተሟጋች ግሪን ፒስ አስታወቀ፡፡
ግሪን ፒስ ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው÷ መኪና አምራች ኢንዱስትሪዎች ብረትን በዋና ግብአትነት መጠቀማቸው ለከፍተኛ የካርበን ዳይ ኦክሳይድ ልቀት ምክንያት ሆነዋል።
የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ በብረት ምርት ላይ ጥገኛ ነው ያለው የግሪን ፒስ ሪፖርት÷በዓለማችን ላይ ያሉ 16 መኪና አምራቾች በፈረንጆቹ 2022 ከ39 እስከ 65 ሚሊየን ቶን ብረት መጠቀማቸውን ጠቅሷል።
የጃፓኑ ቶዮታ ኩባንያ በ2022 ብቻ 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን ብረት መጠቀሙን የገለጸው ሪፖርቱ፥ የጀርመኑ ቮልስዋገን 5 ነጥበ 2 ሚሊየን ቶን እንዲሁም የደቡብ ኮሪያው ሃዩንዳይ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን መጠቀማቸውን አስታውቋል።
በእነዚህ ኩባንያዎች በሚደረገው ከፍተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት ምክንያት የዓለም የሙቀት መጠን ወደ 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ወይም 2 ነጥብ 7 ዲግሪ ፋራናይት ከፍ ማለቱ ነው በሪፖርቱ የተገለፀው፡፡
በዚህ ሳቢያም ዓለምን ወደ ጥፋት እየመሯት ነው ብሏል በሪፖርቱ።
የአውሮፓ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች የብረት አቅርቦት ሰንሰለታቸውን ከካርበን ነፃ ለማድረግ መሞከራቸውን የገለፀው የግሪን ፒስ ሪፖርት ነገር ግን ጥረታቸው አልተሳካም ብሏል፡፡
አሁን ላይም ለቸግሩ እልባት ለመስጠት 60 በመቶ የሚሆነው የዓለም የብረታብረት ምርት በሚገኝበት የምስራቅ እስያ ክፍል ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል መባሉን አልጀዚራ ዘግቧል።