ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናከራ ትቀጥላለች – በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃፓን በኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን አርሲ ነገሌ ወረዳ በ13 ሚሊየን ብር በጃፓን መንግስት ድጋፍ የተገነባው የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከል ተጠናቆ ርክክብ ተደርጓል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያና ጃፓን ግንኙነት ከ65 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው።
በእነዚህ ዓመታትም የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ የሚከናወኑ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ሲደግፍ ቆይቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በምዕራብ አርሲ ዞን ‘ጡርጌ ጋሎ’ ቀበሌ የተገነባው የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕክል ወይም ‘ኤፍ.ቲ.ሲ.’ የዚሁ የልማት ትብብር ማሳያ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በቀጣይም ተመሳሳይ ፕሮጄክቶችን በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በማስፋፋት ጃፓን የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል እና ግብርናውን ለማዘመን የተጀመረውን ስራ መደገፏን ትቀጥላለችም ነው የተባለው፡፡