የሀገር ውስጥ ዜና

ሲሪላንካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች

By Alemayehu Geremew

May 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሲሪላንካ ግንኙነቷን ከኢትዮጵያ ጋር ማጠናከር እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የሲሪላንካ አምባሳደር ቴሻንታ ኩማራሲሪ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የሲሪላንካ አምባሳደር ቴሻንታ ኩማራሲሪ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ አስረክበዋል፡፡

የሲሪላንካ ፕሬዚዳንት ራኒል ዊክሪሜሲንግ ÷ “አፍሪካን ተመልከቱ” በሚል መሪ ቃል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ማደሳቸውን እና ግንኙነታቸውን ከአኅጉሩ ጋር በአዲስ መንፈስ ለማጠናከር እየሠሩ እንደሆነ አምባሳደር ቴሻንታ ለፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ መንግስት ከሲሪላንካ መንግስት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ብሎም ለጋራ ጥቅም የሚበጅ የባለ ብዙ ወገን ትብብር ለመመሥረት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ውይይታቸው በተለይ በሀገራቱ መካከል የንግድ እና የኢንቨስትመንት አጋርነት መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን ከፕሬዚዳንት ጽኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የሀገራቱ ባለሐብቶች በአልባሳት ምርት ፣ ቱሪዝም፣ መስተንግዶ ፣ ግብርና፣ አይ.ሲ.ቲ፣ ፈጠራ ፣ ሎጂስቲክስና ግንባታ ዘርፎች ላይ ቢሠሩ አዋጭ መሆኑን መክረዋል።

ሁለቱ ወገኖች የአየር ንብረት ለውጥን ያማከሉ ሰማያዊ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ተኮር ዘላቂ የልማት ዕቅዶቻቸው ላይ እንዲሁም አካታች የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ በሚያስችሉ ሰፊ አፍሪካን ያማከሉ አጋርነቶች እና ዕቅዶች ላይም ተወያይተዋል፡፡