ዓለምአቀፋዊ ዜና

በሱዳን የተኩስ አቁም ሥምምነቱ ለተጨማሪ 5 ቀናት ተራዘመ

By Alemayehu Geremew

May 30, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የተኩስ አቁም ሥምምነቱን ለተጨማሪ 5 ቀናት አራዘሙት፡፡

የሱዳን ጦር እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል አዲስ ስምምነት ላይ የደረሱት በፈረንጆቹ ግንቦት 20 ቀን 2023 በሳዑዲ አረቢያ መዲና ጅዳ ከመከሩ በኋላ መሆኑን ሺንዋ አል-አረቢያን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

ሁለቱ ኃይሎች ሠላማዊ ዜጎች ከጦርነት ቀጣናው ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት መንገድ በመክፈት ለማሳለጥ ሥምምነት ላይ መድረሳቸውም ነው የተመላከተው፡፡

ተፋላሚዎቹ ከጦርነት ቀጣናው ሸሽተው የሚወጡ ነዋሪዎች ያለ ሐሳብ ከጓዛቸው ጋር እንዲንቀሳቀሱ ሥምምነት ላይ ደርሰዋልም ነው የተባለው፡፡

የአሁኑ የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ሥምምነት እና የሰብዓዊነት ምላሽ በፈረንጆቹ ግንቦት 6 ላይ በሳዑዲ እና በአሜሪካ አነሳሽነት የተጀመረው በሱዳን ዘላቂ ሠላም የማስፈን ጥረት ማሳያ ነው ተብሏል፡፡