በአፋር ክልል 196 የውሃ ተቋማት ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በነበረው ችግር በአፋር ክልል ጉዳት የደረሰባቸው 196 የውሃ ተቋማት ጥገና ተደርጎላቸው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ ሻሚ የውሃ ተቋማቱን መልሶ በማቋቋም ለአገልግሎት ማብቃት የተቻለው የክልሉ መንግስት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መሆኑን ገልፀዋል።
ተጠግነው ለአገልግሎት የበቁት ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩ 293 የውሃ ተቋማት መካከል መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው÷ የቀሩት የውሃ ተቋማት ወደ ነበሩበት ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ለተጠገኑት የውሃ ተቋማት 356 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰው÷ በዚህም ከ831 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል እንደተቻለ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከነበረው ችግር ጋር ተያይዞ ከጥልቅ ጉድጓዶች ውሃ የሚሳብባቸው በነዳጅ የሚሰሩ ጀኔሬተሮች በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት አገልግሎቱን ለማስቀጠል አስቸጋሪ በመሆኑ በፀሐይ ሃይል በሚሰሩ የመተካት ስራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።