የሽብር ተግባር ለመፈፀም በማቀድ ቦምቦችን በቤት ውስጥ ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የ15ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ተግባር ለመፈፀም በማቀድ 10 ቦምቦችን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት በቤት ውስጥ ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የ15ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።
ለዐቃቤ ሕግ የክስ መመስረቻ ጊዜ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ተጠርጣሪዎቹ ሕገ -መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በኢ- መደበኛ አደረጃጀት ተደራጅተው የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማቀድ 10 ቦምቦችን ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በማምጣት በየካ ክፍለ ከተማ በተከራዩበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ቦምቦችን ደብቀው ተይዘዋል ባላቸው ሞላልኝ ሲሳይና አብርሐም ጌትነት በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ሲያከናውን የቆየውን ምርመራን ማጠናቀቁን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስታውቋል።
የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለኝ የ15 ቀን የክስ የመመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ በማለት የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው፥ ”የጦር መሳሪያ ይዞ የመገኘት ወንጀል የዋስትና መብት ስለማያስከለክል ፍርድ ቤቱ ይህን ተገንዝቦ የዋስትና መብታቸውን ይፍቀድልን ”ሲሉ ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ በሽብር ወንጀል ተግባር እንጂ የተጠረጠሩት በጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት አይደለም፤ ምርመራ እየተከናወነባቸው ነው በማለት መልስ ሰጥቷል።
በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ቦምቦቹን ለሽብር ወንጀል ተግባር ለማዋል ወደ አዲስ አበባ በማምጣት በቤት ውስጥ ደብቀው ስለመያዛቸው በተረከብነው መዝገብ ላይ ለመረዳት ችለናል ሲል በጠበቆች የተጠየቀው ዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግለት የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት የ15 ቀን ጊዜ እንደሚያስፈልግ በማመን የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የ15 ቀን የክስ የመመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ