ብሔራዊ የኮቪድ-19 ልዩ የጥናትና ምርምር ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኮቪድ-19ን አስመልክቶ ጥናትና ምርምር በማካሔድ ምክረ ሀሳቦችን የሚያቀርብ ልዩ ግብረ-ሀይል አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።
ግብረ ሀይሉ “ብሔራዊ የኮቪድ-19 ልዩ የጥናትና ምርምር ግብረ ሀይል” ሲሆን፥ በግብረ ሀይሉ ውስጥም የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን፣ ተቆጣጣሪ አካላትን፣ የሳይንስ ሙያ ማህበራትን እና የሳይንስ ጥናትና ምርምር የሚሰሩ የውጭ ሀገር ድርጅቶች ተካተዋል።
ግብረሀይሉ የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የተቋቋመ መሆኑን የገለፁት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ ከግብረሀይሉ አባላት ጋር ምክክሮች በበቴክኖሎጂ በመታገዝ ቨርቹዋሊ እንደተካሄዱ ገልጸዋል።
የዚህ አይነቱ የተለያዩ የሳይንስና ምርምር ተቋማትን በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማሰባሰብ ተቀናጅቶ መስራት ከማንኛዉም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት አስፈላጊ እንደሆነ እና ለወደፊቱም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ፕሮፌሰር አፈወርቅ አክለውም፥ ሀገራዊ የኮቪድ-19 ጥናትና ምርምር ስራ ሁሉንም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመለከት እንደመሆኑ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች “የኮቪድ-19 ልዩ የጥናትና ምርምር ግብረሀይል” ተቋቋሞ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንቶች እየተመራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
እንደ ዩኒቨርስቲው ተጨባጭ ሁኔታም በሁሉም ትምህርት መስኮች ሊዳሰሱና ሊሰሩ በሚገቡ የምርምር ጉዳዮች እና በተለያዩ ትምህርት ክፍሎች በቅንጅት ሊሰሩ የሚገቡትንም በመለየት በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅድ እንዲመራ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።
በየግብረሀይሉ የሚከናወኑ የትግበራ ውጤቶችም በቀጣይ በኮቪድ-19 ዙሪያ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዘጋጅነት በሚካሄዱ ሳምንታዊ የምሁራን ውይይት መድረኮች ላይ እየቀረቡ ለባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ ተደራሽ እንደሚደረጉም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።