በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ 86 ተጋላጭ ፍልሰተኞችን ወደ ሀገራቸው መለሰ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጅቡቲ ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ቢሮ ጋር በመተባባር 86 ፍልሰተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ገለጸ።
ከፍልሰተኞች መካከል 30 ያህሉ በየመን በአስከፊ ችግር ውስጥ ቆይተው ወደ ጅቡቲ የገቡ ሲሆኑ÷ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመሻገር ጅቡቲ ከገቡ በኋላ ባህር የመሻገር ሐሳባቸውን ለመቀየር የተገደዱ ናቸው ተብሏል፡፡
በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በመካከኛው ምሥራቅ አገራት በአጭር ጊዜ ለመክበር በሚል የቀቢጸ ተስፋ ምኞት ተታልለው እና ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ከሀገራቸው የወጡት ፍልሰተኞቹ በመሸጋገሪያ እና መዳረሻ ሀገራት ለረሃብ፣ ለውኃ ጥም፣ ለጤና መታወክ፣ ለከፍተኛ እንግልት እና ተያያዥ ችግሮች የተዳረጉ መሆናቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከኢትዮጵያ-ጅቡቲ-የመን የሚደረገው ሕገ-ወጥ የሰዎች ፍልሰት በሞት እና ልዩ ልዩ አደጋዎች የተሞላ በመሆኑ፣ ኤምባሲው የኢትዮጵያ ወጣቶች በሕገ-ወጥ ደላሎች የውሸት ስብከት በመታለል ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ መልዕክት አስተላልፏል።