የሶማሌ ክልል ስፖርትን ለማስፋፋትና ለማልማት በትኩረት እየሰራ ነው – አቶ ሙስጠፌ መሃመድ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ስፖርትን ለማስፋፋት እና ለማልማት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ጋር በክልሉ ስፖርት እንቅስቃሴ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በዚሁ ወቅት ÷ ስፖርት ከመዝናኛነት ባሻገር ለፖለቲካና ኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉ ስፖርትን ለማስፋፋትና ለማልማት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀው ÷ በክልሉ ባሉ ዞኖች አራት ስታድየሞችና አንድ ሁለገብ የወጣቶች ማዕከል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የጂግጂጋን ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በቀጣይ ዓመት ለማስጀመር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክልሉን በብሔራዊ ሊጎች በተለይም በፕሪሚየር ሊግ የሚወክል ተወዳዳሪ ክለብ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ስፖርትን ለሰላም ከማዋል አንፃርም ከምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ጋር የስፖርት ውድድርና ፌሲቲቫል ለማዘጋጀት ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ÷ ዘርፉ የሚፈልገው ሃብት በመንግስት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ የግሉን ዘርፍና ህዝቡን በማሳተፍ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በተጨማሪም የክልሉ ህዝብ ሀብት የሆነውን ባህልና ኪነጥበብ በማስተዋወቅ ረገድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል።
በውይይቱ የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረ/ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ እና የአትሌቶች ማህበር ኘሬዚዳንት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነቴም ተገኝተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ በጂግጂጋ ከተማ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መጎብኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።