ዓለምአቀፋዊ ዜና

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የዛፓሮዢያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ደኅንነት ያሳስበኛል አለ

By Alemayehu Geremew

May 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የዛፓሮዢያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ደኅንነት እንደሚያሳስበው አስታወቀ፡፡

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋዔል ማሪያኖ ግሮሲ ለተመዱ የደኅንነት ምክር ቤት እንደገለጹት ÷ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫው ሩሲያና ዩክሬን በሚፋለሙበት ግንባር አቅራቢያ መገኘቱ የደኅንነቱን ሁኔታ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በአካባቢው ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ አለመሆኑንም አስገንዝበዋል።

ማሪያኖ ግሮሲ ÷ “እስካሁን የኒውክሌር አደጋ ባለመከሰቱ ዕድለኞች ነን ፤ በአካባቢው ያለው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ግን አንድ ቀን ዕድላችን ያበቃል” ሲሉም ነው የሁኔታውን አሳሳቢነት የገለጹት።

በኒውክሌር ማብላያው አካባቢ ከሁለቱም ወገኖች የሚቃጣ ምንም ዓይነት አደጋም ሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማድረግ እንደሚገባ መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል።

በማብላያው አካባቢ እንደ ታንክ ያሉትን ከባድ የጦር መሳሪያዎች ማከማቸት ዋጋ እንደሚያስከፍልም ነው የተናገሩት፡፡

በሠላሙ ጊዜ የዛፓሮዢያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለዩክሬናውያን 1/5 የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በማመንጨት የሚሸፍን ነው፡፡

በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከተገነቡ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ግማሽ ያህሉን የኃይል አቅርቦት ብቻውን በመሸፈንም ይታወቃል፡፡

ማመንጫው በደቡብ-ምሥራቅ ዩክሬን ኤነርሆዳር ውስጥ ድኒፐር ወንዝ ላይ ተገንብቶ ይገኛል፡፡