Fana: At a Speed of Life!

የሚሸጥበትን 400 እጥፍ ገንዘብ ለዕድሳት የሚጠይቀው ጥንታዊ ቤተ መንግስት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በስኮትላንድ ግዛት ሼትላንድ ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊ ቤተ መንግስት ለጨረታ ቢቀርብም ከግዢ በኋላ የሚጠይቀው ወጪ ግን መነጋገሪያ ሆኗል።

የቤት ገዢዎች በፌትላር ደሴት የሚገኘውን ቤተ-መንግስት÷ ከአንድ ወለል ህንፃ ባነሰ ዋጋ በእጃቸው የሚያስገቡበት አጋጣሚ መፈጠሩ ተነግሯል።

ቤተ መንግስቱ በ30 ሺህ ፓውንድ ለገበያ መቅረቡ የበርካቶችን ቀልብ ቢስብም ከገዙት በኋላ ለዕድሳት የሚፈልገው ወጪ ግን እጅግ የተጋነነ መሆኑ ተጫራቾች ግዢውን እንዲያስቡበት ማድረጉ አልቀረም።

ምክንያቱም ይህን ጥንታዊ ቤተ መንግስት በ30 ሺህ ፓውንድ የሚገዛ አካል ለአጠቃላይ ዕድሳቱ 12 ሚሊየን ፓውንድ ማውጣት ግድ ይለዋልና ነው።

ይህ ደግሞ ገዢው አካል ንብረቱን ከገዛበት 400 እጥፍ ዋጋን ለዕድሳት እንዲያወጣ ያስገድደዋል።

የ200 ዓመት ዕድሜ ያለው ይህ ቤተ መንግስት በ16 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን÷ ማማዎች፣ የታጠረ ሰፊ ግቢ እና የአትክልት ስፍራዎች ያሉት መሆኑ ተጠቁሟል።

ነገር ግን የሚገዙት ባለሀብቶች በፈረንጆቹ 1820 የተገነባውን ሕንፃ የእድሳት ወጪ ለመሸፈን የደለበ ኪስ እንደሚያስፈልጋቸው ከወዲሁ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ቢቢሲ ዘግቧል።

በስኮትላንድ ካለው አማካይ የቤት ዋጋ አንፃር 30 ሺህ ፓውንድ በእጅጉ ያነሰ ሲሆን÷ ንብረቱ ባለፈው አመት በነሐሴ ወር ላይ በተደረገ ምዝገባ ከ195 ሺህ ፓውንድ በላይ በሆነ ዋጋ የተሰላ መሆኑ ተመላክቷል።

ህንፃውን ለመንከባከብ በፈረንጆቹ 1998 የተመሰረተው ብሮው ሎጅ ትረስት ስራ ፈጠራ ተቋም ቦታውን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እቅድ እንዳለውና ያንንም ለማሳካት ተማጽኖ ማቅረቡ ተነግሯል።

ሎጅው ያቀረበው ሃሳብም ነባሩን ሕንፃ ባለበት ይዞ ሌላ 24 መኝታ ቤቶችን እና ሬስቶራንትን ጨምሮ ማደስን መጨመር የሚያካትት መሆኑ ነው የተጠቆመው።

ራዕዩ ቀላል እና ውጤታማ እንደሆነ የሚገልፀው ሎጅው ባዘጋጃቸው ዕቅዶች መሠረት የሕንፃው ታሪካዊ ቅርስነት ሙሉ በሙሉ እንደሚከበር በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ አስረድቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.