የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በሚሊኒየም አዳራሽ በመዘጋጀት ላይ ያለውን የኮቪድ 19 የህክምና መስጫ ማዕከል ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ በሚሊኒየም አዳራሽ በመዘጋጀት ላይ ያለውን የኮቪድ 19 የህክምና መስጫ ማዕከል ጎበኘ።
በጉብኝቱ ወቅት የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ኢስማኤል ሸምሰዲን ለቦርዱ አባለት የማዕከሉን ዝግጅት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ማዕከሉ 1 ሺህ ህመምተኞችን የሚይዝ የመኝታ፣ ከታካሚዎች ንኪኪ ነጻና የራሱ መግቢና መውጫ ያለው፣ የምግብ ማብሰያ፣ የላብራቶሪና የላውንደሪ ክፍሎች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል።
28 አልጋዎች ለፅኑ ህሙማን (ICU) መዘጋጀታቸውንና 17 ቬንትሌተር በዛሬው እለት እንደሚገጠምላቸውም ተናግረዋል።
በተጨማሪም አዳራሹ 6 በሮች ያሉት በመሆኑ የህመምተኞች መግቢና መውጫ ተለይቶ መዘጋጀቱን፣ ታካሚዎች በእግር እንዲንቀሳቀሱ ሰፊ ኮሊደር እንዲኖረው መደረጉን፣ የከፋ ችግር ቢከሰት ሌሎች 1 ሺህ አልጋዎችን የሚይዝ ሰፊ ቦታ መኖሩንም ገልጸዋል።
ታካሚዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ስለማይችሉ በስካይፒ በታብሌቶች እንዲገናኙ ለማድረግ እንዲሁም እንዲዝናኑና መረጃዎችን እንዲያገኙ ቴሌቪዥኖችን የመግጠም ስራዎች እንደሚሰሩም አክለዋል።
የህክምና ማዕከሉ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለመድረግም ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ማብራራታቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የቦርዱ አባላት በጉብኝቱ ማብቂያ ላይ በሰጡት አስተያየት በአጭር ጊዜያት ውስጥ እነዚህ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አድንቀዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት፥ በማዕከሉ በኩል በእጥረት የተነሱ ነጥቦችን ቦርዱ ነቅሶ በማውጣትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሚፈቱበትን መንገድ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።
እስካሁን የተከናወኑት ተግባራት በእጅጉ ሊበረታቱ የሚገባና ለክልሎችም ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችን በመግለፅ፤ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆንም በቀጣይም ተቀናጅቶ የመስራቱ ሁኔታ የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።