Fana: At a Speed of Life!

የጨጓራ ቁስለት መንስኤ እና ህክምናው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨጓራ ቁስለት ብዙውን ጊዜ የሚያጠቃው ጨጓራን እና ከጨጓራ ቀጥሎ ያለውን ትንሹን የአንጀት ክፍል ነው፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጨጓራ ቁስለት መንስኤና ህክምናውን በተመለከተ ከውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ሚፍታ ደሊል አህመድ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ዶክተር ሚፍታ እንደሚሉት ፥ ጨጓራ ምግብ የመፍጨት ሂደቱን ለማመቻቸት አሲድ እና ሌሎች መፍጫ ኢንዛይሞችን የሚያመነጭ ሲሆን ፥ ከፕሮቲን የተሰራው ጨጓራ እራሱን በራሱ እንዳይፈጭ የሚከላከልበት የራሱ መንገድ አለው፡፡

ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ አንዱ ከተጓደለ ወይም አሲድ ከበዛ የጨጓራ ቁስለት ሊከሰት ይችላል፡፡

ባክቴሪያ ሌላው የጨጓራ ቁስለት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል አበንስተውም ፥ ባክቴሪያ ጨጓራ እራሱን መከላከል የሚችልበትን አቅም በማሳጣት በአሲድ እና በኢንዛይሞች እንዲጠቃ በማድረግ የጨጓራ ወይም የአንጀት ቁስለት እንዲከሰት ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ሌላው የአንጀት ቁስለት መንስኤ ለረዥም ጊዜ እንደ አስፕሪን ፣ኢቡፕሮፈን ፣ዳይክሎፌናክ መሰል የማስታገሻ መድሃኒቶችን ለረዥም ጊዜ መጠቀም ነው ይላሉ ባለሙያው ፡፡

መጨነቅ፣ በከፍተኛ ህመም ምክንያት ጽኑ ህሙማን ህክምና ውስጥ መቆየት፣ የመቃጠል አደጋ፣ የመኪና አደጋ በሚፈጠርበት ጊዜም ወደ ጨጓራ የሚሄደው ደም ስለሚቀንስና ጨጓራ እራሱን መከላከል ስለማይችል በቀላሉ የመቁሰል ነገር ያጋጥመዋል፡፡

የጨጓራ ቁስለት ምልክቶች በጣም ብዙ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር ሚፍታ ፥ ደረት ስር የማቃጠል ስሜት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ የምግብ ያለመፈጨት ችግር፣ ደም ማስቀመጥ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ይላሉ፡፡

በተለይም ÷ ማስመለሱ ጠቆር ያለ የቡና አተላ የመሰለ ፈሳሽ ካለው፣ ሰገራ በጣም ከጠቆረ እና ደም የተቀላቀለበት ከሆነ ከባድ የጨጓራ ቁስለት ምልክት ስለሆነ ታማሚው ቶሎ የህክምና ባለሙያ ማናገር አለበት ይላሉ፡፡

አብዛኛው ጊዜ የአንጀት ቁስለት የሚከሰተው የመጨረሻው የጨጓራ ክፍልና የመጀመሪያው የትንሹ አንጀት ክፍል ሲሆን ፥ በተደጋጋሚ መቁሰልና መዳን በሚከሰትበት ጊዜ ቁስሉ ጠባሳ እየፈጠረ ስለሚሄድ የጨጓራ መዘጋት ወይም የአንጀት መዘጋት ሊፈጥር ይችላል ነው ያሉት፡፡

አንድ የጨጓራ ቁስለት ታማሚ ማስመለስ ፣ ከፍተኛ የክብደት መቀነስና የደም ማነስ ምልክቶች ከታዩበት የከባድ ጨጓራ ቁስለት ምልክቶች ስለሆኑ በአስቸኳይ ወደጤና ተቋም ሄዶ መታየት እንደሚያስፈልግ ባለሙያው አመላክተዋል፡፡

የጨጓራ ቁስለት ያለባቸው ሰዎች በተለይ ቁስለቱን የማከምያ መዳኒት እየወሰዱ ከሆነ ህመማቸው እንዳይባባስ ሲጋራ ፣ አልኮል፣ ቡና ሻይና የመሳሰሉ ነገሮችን ማቆም እንዳለባቸውም ይመክራሉ፡፡

ምግብ በስዓቱ መመገብና በአንዴ አብዝቶ አለመመገብ አንዱ የጨጓራ ቁስለት እንዳይባባስ ማድረጊያ ዘዴ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.