Fana: At a Speed of Life!

ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይ እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ኅብረተሰቡን ለማሳሳት ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ÷ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመሥጠት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምበት የነበረውን ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራን መዝጋት መሆኑን አስታውሷል፡፡

ነገር ግን ሰሞኑን አንዳንድ ግለሰቦች በማሕበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በተጠርጣሪዎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ፈጽሟል እያሉ የተቋሙን መልካም ሥም ለማጠልሸት ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ እንደሚገኙ በመረጃው አንስቷል፡፡

ይህንን መሠረተ-ቢስ ውንጀላ እየፈጸሙ ያሉት በአሸባሪነት ተጠርጥረው እንደሚፈለጉ እና ሥም ዝርዝራቸውም ለሕዝብ በይፋ ከተገለጹት መካከል መሆናቸው እንደተደረሰበት ጠቁሟል፡፡

ፌዴራል ፖሊስ ÷ ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በሽብር ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ግለሰቦች ላይ እያካሄደ ያለውን ምርመራ ለማደናቀፍ ነው ብሏል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአሸባሪዎች ላይ የጀመረውን የምርመራ ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸ ፣ ኅብረተሰቡ ሐሰተኛ ወሬ ሳይደናገር ትክክለኛው መረጃ በቦታው ተገኝቶ ከፖሊስ እና ከተጠርጣሪዎች አንደበት ማረጋገጥ እንደሚችል አስታውቋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.