Fana: At a Speed of Life!

ሀገራት በሳይበር ምህዳሩ ዘላቂ ጥቅም እንዲያገኙ ትውልድ ተሻጋሪ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት ይገባል – አቶ ሰለሞን ሶካ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳይበር መህዳሩ የፈጠረው መልካም አጋጣሚ ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀምና ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት በትውልዶች መካከል የአስተሳሰብ ትስስርና የእውቀት ሽግግር ማድረግ ወሳኝ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ፡፡

በጂ አይቲክስ አፍሪካ አውደ ርዕይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ÷በትውልድ መካከል የሚፈጠሩ የእውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

የሳይበር ምህዳር ላይ የተሰማሩ ተቋማት ካለው የበቃ የሰው ሃይል እጥረት ጋር ተያይዞ ለሰው ሃይል ልማት ከፍተኛ ቦታ መስጠት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

አቶ ሰለሞን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን (የኢመደአ) የሰው ሃይል ልማት ሂደቶች በሶስት ትውልድ ደረጃዎች ከፍለው ገለጻ አድርገዋል፡፡

የመጀመሪያው ትውልድ ስለሳይበር ጉዳይ በትምህርት ላይ የተመሰረተ ብዙ እውቀት ባይዝም የሀገራዊ ፍላጎቶችን በደንብ በመረዳትና በከፍተኛ ሃገራዊ ፍቅር ራሱን ከሁኔታዎች በማጣጣም እንደ ሃገር አቅም ባልተፈጠረባቸው ዘርፎች የአመራር ክህሎቱን የሚጠቀም መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህም ለሁለተኛው ትውልድ ግልጽ አመራር በመስጠትና እርሾ ሊሆን የሚችል ሀገራዊ አቅም እንዲፈጠር አስቻይ ሚና የተጫወት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ ከትምህርት ቤት ካገኘው እውቀት ባሻገር እንደተቋም ለሰው ሃይል አቅም ግንባታ ከተሰጠው ትኩረት አንጻር የተለያዩ የስልጠና እድሎችን እንዲሁም በሀገራዊ ፕሮጀክቶች ቀጥታ የተግባር ተሳትፎ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የቴክኒካል አቅም እንዲገነቡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው ወሳኝ የሀገር አቅም የሆነ ትውልድ ሲሆን÷ ከቀደምቶቹ ልምድ በመቅሰምና በመማር ተቋሙን እንደተቋም ሃገርን እንደሃገር በሚያደርጋቸው ጥረቶች የተለያዩ አበርክቶዎችን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሶስተኛው ትውልድ በተቋሙ የሳይበር ደህንነት ታለንት ልማት ማዕከል የታቀፉ ታዳጊዎችን ያቀፈው ትውልድ ሲሆን÷ ሁለተኛው ትውልድ ላይ ብቻ መንጠልጠል ተገቢውን የዲጂታል ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ከባድ ስለሚሆን በታለንት ልማትና ልህቀት ላይ መስራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰው ሃይልን ከትምህርት የተመረቁ አካላትን ብቻ ይዘን የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ቀጣይነት ያለውን የበቃ የሰው ሃይል ልማት ማስቀጠል ስለማይቻል ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎች መልምሎ እና እውቀታቸውን አጎልብቶ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሳይበር ጥቃት ከዓለማችን ቀዳሚ ስጋቶች አንዱ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ከምህዳሩ ፍጹም ተለዋዋጭና ኢ-ተገማችነት አንጻር አንድ ሃገር ብቻውን ምንም ሊፈጥር ስለማይችል ሀገራት በሳይበር ምህዳሩ ላይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.