ፋና ስብስብ

4 ባለ ተሰጥኦ ድምፃውያን የፊታችን ቅዳሜ በፋና ላምሮት 1 ሚሊየን ብር ለመካፈል ይወዳደራሉ

By Alemayehu Geremew

June 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አራት ባለ ተሰጥኦ ድምፃውያን የፊታችን ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ሚሊየን ብር ላይ ከፍተኛውን ሽልማት ለመውሰድ በፋና ላምሮት ይወዳደራሉ።

በዚህም ሐብታሙ ይሄነው፣ ግርማ ሞገስ፣ በረከት ደሞዝ እና ዘውዱ አበበ በፋና ላምሮት ምዕራፍ 13 የባለተሰጥኦ ድምፃውያን የፍጻሜ ተወዳዳሪዎች ናቸው።

በምዕራፍ 13 የፋና ላምሮት የባለተሰጥዖ ድምፃውያን የፍፃሜ ውድድር ላይ ከዛየን ባንድ ጋር ሆነው ቅዳሜ ይነግሳሉ፡፡

ውድድሩም በፋና ቴሌቭዥን በቀጥታ ሥርጭት የሚተላለፍ ይሆናል፡፡

በፍፃሜው ውድድር ተወዳዳሪዎቹ የሙዚቃ ሥራቸውን በ3 ዙር ያቀርባሉ፡፡

በዕለቱ ከመደበኛ ዳኞች በተጨማሪ አንድ አንጋፋ እና ተወዳጅ ድምፃዊ በእንግዳነት በመገኘት ውድድሩን ይዳኛል።

ከዚህ ቀደም በየምዕራፉ 500 ሺህ ብር ይካፈሉ የነበሩት የፍፃሜ ተፋላሚዎች አሁን ሽልማታቸው ወደ 1 ሚሊየን ብር ከፍ ብሏል።

በመሆኑም በውድድሩ ÷ 1ኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው 400 ሺህ ብር 2ኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው 300 ሺህ ብር 3ኛ ይዞ የሚያጠናቅቀው 200 ሺህ ብር እንዲሁም 4ኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው ተወዳዳሪ ደግሞ የ100 ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል።

እነዚህ አራት ተወዳዳሪዎች በእርግጥ ለዋናው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ማለፋቸውን ከወዲሁ አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ማለትም በምዕራፍ 14 እና 15 ለፍፃሜ ከሚቀርቡ ተወዳዳሪዎች ጋርም ዳግም በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ይመለሳሉ።

የፊታችን ቅዳሜ በምዕራፍ 13ቱ የፍፃሜ ውድድር ላይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ከ6 ሠዓት ጀምሮ በቀጥታ ሥርጭት ተመልካቾችን ይጠብቃል።

ፋና ቴሌቪዥን በዕለቱ የሚገለጸውን የተወዳዳሪዎችን ኮድ በ8222 በመላክ አሸናፊ መሆን ይገባዋል የምትሉትን መምረጥ ትችላላችሁ ሲል ከወዲሁ ያበስራል።