በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ የልማት ሥራዎች ሊቀጥሉ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉም ጥረት ሊታከልበት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ለጎብኚዎች ክፍት የሆነው የግብርና ሳይንስ አውደ-ርዕይ በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች ታዳሚዎች እየተጎበኘ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዛሬው መርሐ-ግብር ላይ የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ተገኝተው በኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴና በአረንጓዴ ልማት መርሐ-ግብሮች ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኖቸውን ተናግረዋል፡፡
በኩታ-ገጠም እርሻ እና በግብርና ሜካናይዜሽን ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን ለመቻል እና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኗንም አንስተዋል፡፡
እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ቅመማ ቅመም፣ ማርና የእንስሳት ተዋጽኦ ያሉትን በአግባቡ ማልማት ከተቻለ ሀገር መለወጥ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ኢትዮጵያ ሐብቷን ማልማት ከቻለች እድገትና ብልጽግናዋን በአጭር ጊዜ ማሳካት ያስችላልም ነው ያሉት።