የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ልዑክ በቻይና የስራ ጉብኝት እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ እና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ከሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በቻይና ቤጂንግ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡
በጉብኝቱ ቻይናውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሰማሩ ማድረግ በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
ለዚህም አጠቃላይ የመንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች ላይ እና በሀገሪቱ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን አስመልክቶ ለባለሃብቶች ገለጻ ተደርጓል፡፡
ልዑኩ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲም ጉብኝት ያደረገ ሲሆን÷በቻይና ከኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው ጋር ስለ ኢንቨስትመንት ምልመላ ስራዎች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ስለኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ የማሻሻያ ተግባራትና የስራ እንቅስቃሴ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ባለፉት 9 ወራት ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ልዑኩ በቆይታው በቻይና የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን እና የኢንቨስትመንት ቦታዎችን እንደሚጎበኙ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡