Fana: At a Speed of Life!

12ኛው የቻይና – አፍሪካ የምሁራን ጉባኤ በቻይና እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 12ኛው የቻይና – አፍሪካ የምሁራን ጉባኤ በቻይና ዢኑዋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጉባኤው ከ45 ሀገራት የተውጣጡ ወደ 200 የሚጠጉ ምሁራን እና የቢዝነስ ተወካዮች ሃሳቦችን አቅርበዋል።

ለ12 ተከታታይ ዓመታት የቻይና – አፍሪካ የምሁራን ጉባኤ በአፍሪካ የሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎች ውጤታማ ፖሊሲዎችን እንዲነድፉና እንዲያወጡ እንዳገዛቸው ተገልጿል።

የጉባኤው አስተናጋጅ የዢ ጂያንግ ግዛት ተወካይ ጉዋን ያንግ ቻይና የአፍሪካን ጉዳዮች በአፍሪካዊ መንገዶች እንዲፈቱ ሁልጊዜም ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

ከደቡብ አፍሪካ ተወካይ ዳሪል ስዋንፖኤል ፥ የንግድ ልውውጦቹ ጤናማ በሆኑ የንግድ ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱ ናቸው ብለዋል፡፡

በቻይና ጉምሩክ መረጃ መሰረት ባለፈው ዓመት የቻይና – አፍሪካ የንግድ ልውውጥ ከ280 ቢሊየን ዶላር በላይ ሆኖ ተመዝግቧል።

ወደ አፍሪካ የሚላከው ምርት በዓመት ከ11 በመቶ በላይ የጨመረ ሲሆን ፥ ከአህጉሪቱ የሚገቡ ምርቶችም በተመሳሳይ መጠን ጨምረዋል ነው የተባለው።

የጋምቢያ የከፍተኛ ትምህርት፣ ምርምር፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፒየር ጎሜዝ ፥ ቻይና ከብዙ ዓመታት በፊት ተማሪዎችን ወደ ውጭ በመላክ እንዲማሩ በማድረጓ አዲሲቷን ቻይና እንደገነባችም ገልጸዋል።

በዚህም አፍሪካውያን ወደ ቻይና በመሄድ ተምረው አዲሲቷን አፍሪካ እንዲገነቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት በአንድነት ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር መስመር፣ ወደ 100 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ አውራ ጎዳና እና በአህጉሪቱ የሚገኙ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ድልድይና የሃይል ማመንጫዎችን በጋራ መስራታቸውም ተነስቷል።

በፈረንጆቹ 2011 የተመሰረተው የቻይና አፍሪካ የምሁራን ጉባኤ የትምህርትና ሌሎች ተቋማት የመድብለ-ወገን ትብብርን የሚያበረታቱበትና በዓለም ዙሪያ ላሉ አዳጊ ሀገራት ሃሳቦችን የሚነጭበት ትልቅ መድረክ መሆኑ ይጠቀሳል።

በጉባዔው ኢትዮጵያውያን ምሁራንም እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን ፥ በለው ደምሴ (ዶ/ር) በሁለተኛው የምልአተ ጉባኤ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.