Fana: At a Speed of Life!

ዩክሬን ኔቶን ከተቀላቀለች የማይበርድ ቀውስ ይከተላል ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶን) የምትቀላቀል ከሆነ ለዓመታት የማይበርድ ቀውስ ይከተላል ስትል ሩሲያ አስጠንቅቃለች፡፡

አሜሪካ ድርጅቱን በወታደራዊ አጋርነት ትጠራዋለች ያለችው ሩሲያ÷ ነገር ግን ብዙ የአውሮፓ ህብረት ዓባል አገራት የጉዩን አደገኛነት በሚገባ ተገንዝበውታል ብላለች።

ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ዩክሬን የኔቶ ወታደራዊ ጥምረት አባል እንድትሆን ሐሙስ ዕለት የጠየቁ ሲሆን÷ ለአሁኑ አባልነት የማይቻል ከሆነ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ገልፀዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ፥ የዩክሬን ህብረቱን ለመቀላቀል ያላትን ፍላጎት በተመለከተ ተጠይቀው÷ “ይህ የኪየቭ አስተዳደር ያሉትን ችግሮች በድርድር ለመፍታት ዝግጁ አለመሆንን እና አቅመ-ቢስነቱን ያመላክታል” ሲሉ መልሰዋል።

የዩክሬን የኔቶ አባል መሆን ከዋናዎቹ ቁጣ ቀስቃሽ አጀንዳዎች አንዱ ነው ያሉት ፔስኮቭ ይህም ለብዙ አመታት ለሚዘልቅ ችግር ዋነኛ መንስዔ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኔቶ መስፋፋትን እና ወደ ሩሲያ ድንበር መጠጋትን ጨምሮ ከሌሎች እንቅስቃሴዎችም የሞስኮን ጥቅሞች እና ደህንነት ለማረጋገጥ ሀገራቸው እንደምትሰራ ፔስኮቭ አክለው መግለፃቸውን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

ሩሲያ÷ ኔቶ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ የሚያደርገውን መስፋፋት የምዕራቡን ዓለም የሩሲያ ጠላትነት ማሳያ አድርጋ ስትመለከት እንደቆየች እና በአውሮፓ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ ለማይታወቀው ግጭት መቀስቀስ ቁልፍ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.