በአማራ ክልል ወረዳዎች መጋዝን ውስጥ የተቀመጠ የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ እንዲሠራጭ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ወረዳዎች መጋዝን ውስጥ የተቀመጠ የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ በፍትሀዊነት እንዲሠራጭ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለውን የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ሂደት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙባረክ ኤልያስ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው፣ በግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦትና ገጠር ፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግስቱ ተስፋ ጨምሮ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብና ሰሜን ሜጫ ወረዳዎች ተገኝተው የሁለት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሥራ እንቅስቃሴ ምልከታ አድርገዋል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በደጎይ ህብረት ስራ ማህበር 1 ሺህ 365 ኩንታል ዳፕ ማዳበሪያ እንዲሁም በወተት አባይ ህብረት ሥራ ማኅበር 2 ሺህ 800 ኩንታል ዳፕ ማዳበሪያ በመጋዝን ተከማችቶ አግኝተዋል።
የወረዳ አመራሮች ለምን ለአርሶአደሮች እስካሁን እንዳላሰራጩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ የቀረበው ማዳበሪያ አነስተኛ በመሆኑ ለሁሉም አርሶአደር ማዳረስ ስለማንችል ተጨማሪ ማዳበሪያ እስከሚመጣ እየጠበቅን ነው ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከመስክ ምልከታ መልስ በኋላ ከአርሶ አደሮች ጋር የተወያዩ ሲሆን፥ አርሶ አደሮቹ ለበቆሎ ዘር የሚሆን የማዳበሪያ እጥረት እንዳጋጠማቸውና የቀረበውም ቢሆን ስርጭቱ ፍትሀዊ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም ማዳበሪያ በህገ ወጥ መንገድ እየተሸጠ ነው የሚሉና መሰል አስተያየቶችን አርሶ አደሮች አቅርበዋል።
የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ሀገራዊ ችግር መሆኑን ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙባረክ ኤልያስ መንግስት የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከአርሶ አደሩ ጠቃሚ ግብዓት እንደተገኘ አንስተዋል።
የማዳበሪያ ስርጭቱ ፍትሀዊ መሆን እንዳለበትና አንድም ማዳበሪያ መጋዝን ውስጥ ሊኖር እንደማይገባ መናገራቸውን የቢሮውን ሕዝብ ግንኙነት ጠቅሶ አሚኮ ዘግቧል።
የአቅርቦት እጥረቱን ተከትሎ የሚታየው ህገ ወጥ የማዳበሪያ ንግድን አርሶ አደሩ ታግሎ ማስተካከል ይገባዋልም ነው ያሉት።
በግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦትና ገጠር ፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግሥቱ ተስፋ በበኩላቸው፥ የአፈር ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ እየተራገፈ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በቆሎ ከሚዘሩት ውስጥ ለደጋማ አካባቢዎች ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በዚህ ሳምንት 350 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።