Fana: At a Speed of Life!

በህንድ በባቡር አደጋ 261 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰማ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ በደረሰ የባቡር ግጭት 261 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰማ።

 

አደጋው በምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል ኦዲሻ ግዛት ባቡሮች ተጋጭተው የደረሰ መሆኑን ቢቢሲ አስነብቧል።

 

በአደጋው ለህልፈት ከተዳረጉት በተጨማሪ 650 ሰዎች መጎዳታቸውንም ነው የግዛቷ ባለስልጣናት የተናገሩት።

 

በአደጋው ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልም ተሰግቷል።

 

አሁን ላይም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች የነፍስ አድን ስራ እየሰሩ ነው ተብሏል።

 

ህንድ በባቡር አገልግሎት ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ስትሆን በየቀኑም በሚሊየን የሚቆጠሩ ህንዳውያን የባቡር ትራንስፖርትን እንደሚገለገሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።

 

ይሁን እንጅ የባቡር መሰረተ ልማቱ የዘመነ አለመሆኑን ተከትሎ ተደጋጋሚ የባቡር አደጋዎች እንደምታስተናግድ ይነገራል።

 

በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በርካታ የባቡር አደጋዎች የደረሱ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 1981 በቢሃር ግዛት የደረሰውና ከ800 በላይ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው አደጋ በህንድ ከደረሱት የባቡር አደጋዎች የከፋው መሆኑን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.