የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ደመቀ መኮንን የወደፊቱ የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት ብሩህ መሆኑን ገለጹ

By Amare Asrat

June 03, 2023

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ እና ቻይና በመተማመን እና ወዳጅነት ላይ የተመሰረተው ግንኙነት ሀገራቱ ያልተነኩ እድሎችን አሟጦ ለመጠቀም ካላቸው ፍላጎት አንጻር የወደፊቱ ግንኙነታቸው ብሩህ ነው ሲሉ ገለጹ።

 

አቶ ደመቀ መኮንን በቻይና ከነበራቸው ይፋዊ የስራ ጉብኝት ጎን ለጎን ከሲ ጂ ቲ ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

 

በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት ሁሉን አቀፍ፣ አካታች፣ ስትራቴጂያዊ እና በትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።

 

ይህም የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚ ትልሞች ለመደገፍ ጥሩ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

 

አያይዘውም የሀገራቱ ግንኙነት ከጋራ ጥቅም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያበረታታ የአፍሪካን የመልማት ፍላጎት የሚያሳይ እና ለተቀረው የአፍሪካ ክፍል ምሳሌ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

ከዚህ አንጻር የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን እና የቻይና አፍሪካን የትብብር ፎረምን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

 

አቶ ደመቀ በንግግራቸው የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ጉብኝት እና በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ዡ ቢንግ ጥረት፥ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

 

ኢትዮጵያም በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ላይ ተሳትፎ ለነበራቸው አካላት ሚና እውቅና ትሰጣለችም ነው ያሉት።