Fana: At a Speed of Life!

በምሥራቅ ጎጃም መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች እርምጃ ተወስዶባቸው ሴራቸው መክሸፉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ሥላሴ ገዳም መሽገው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ በነበሩት እስክንድር ነጋና ግብረዓበሮቹ ላይ በተወሰደ እርምጃ ክልሉን የማተራመስ ሴራቸው መክሸፉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ለውጊያ ሲውል የነበረው ምሽግ መሰበሩንና በ200 ታጣቂዎችም ላይ እርምጃ መወሰዱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

የታጣቂ ቡድኑ መሪና አስተባባሪ የነበረው እስክንድር ነጋና ጥቂት ግብረዓበሮቹ ከአካባቢው ለመሰወር ቢሞክሩም በዋናነት የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እግር በእግር በመከታተል የተቀናጀ ኦፕሬሽን እያካሄዱ መሆኑንም ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ ÷ “ባልደራስ” በሚል የፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ሲንቀሳቀስ የቆየው እስክንድር ነጋ የተባለው ግለሰብ የሐሳብ የበላይነትን በማረጋገጥ ዓላማውን ማሳካት ሲሳነው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ሲሞክር እንደነበር አስታውሷል፡፡

ግለሰቡ ይህ እንዳልተሳካለት ሲያውቅ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በማቀድ “የአማራ ሕዝባዊ ግንባር” የተባለ አደረጃጀት በመፍጠር ሽመልስ ስማቸው፣ ሰውመሆን ወረታውና መንበሩ ካሴ ከተባሉ ግብረዓበሮቹ እንዲሁም ከሌሎች ጥቂት የክልሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በመቀናጀትና በህቡዕ በመንቀሳቀስ ታጣቂዎችን ሲመለምል፣ ሲያደራጅና ስምሪት ሲሰጥ እንደነበር መግለጫው ጠቁሟል።

ግንባሩን በሀገር ውስጥ ራሱ እስክንድር ነጋ ሲመራው ÷ በውጭ ደግሞ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የተባለ ግለሰብ ሲያስተባብር እንደነበር አንስቷል፡፡

በሀገር ውስጥና በውጭ ሁለቱ በፈጠሩት ትሥሥርም በክልሉ የትጥቅ ትግል በማድረግ ሕዝቡን ወደማያባራ ጦርነት ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ማረጋገጡን አመላክቷል፡፡

መሠረቱን ምዕራብ ጎጃም ቡሬና አባይ በረሃ አካባቢ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግለሰብም ÷ የሃይማኖት ሽፍንን እንደ ከለላ ለመጠቀም ከሌሎች የቡድኑ ታጣቂዎች ጋር ወደ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በማቅናት ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በሥላሴ ገዳም አካባቢ ምሽግ ቆፍረው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል በህቡዕ ሲያሴሩ እንደነበር መግለጫው አመላክቷል፡፡

በተለይም የገዳሙ አስተዳዳሪ የሆኑትን አባ ኤልሳን ለዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲጠቀሙ እንደነበርም ጠቅሷል፡፡ አስተዳዳሪውም ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጭ በገዳሙ ውስጥ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ከመፍቀድ ባሻገር ከሌሎች መነኮሳት ጋር በማበርና የጦር መሣሪያ ጭምር በማንገብ ከጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ጋር ተሰማርተው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡

መግለጫው አክሎም እነዚህ ጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ሕግ የማስከበር ተልዕኮ ለማደናቀፍ በማለም የዜጎችን ሠላማዊ ሕይወት በሚያስተጓጉሉ ቅስቀሳዎችና ተግባራት ተሰማርተው መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡

በአማራና በወለጋ አዋሳኝ አካባቢዎችም ግጭት እንዲቀሰቀስ ሲያደርጉ እንደነበርም አመልክቷል፡፡

የጥፋት ቡድኑ አባላት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴውን እንዲያቆሙና በውይይት ወደ ሠላም እንዲመጡ ከክልል እስከ ወረዳ በሚገኙ አካላት ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም አለመሳካቱን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ገዳሙን ምሽግ በማድረግ በአካባቢው አስተዳደር፣ በፖሊስ ፣ በሚሊሻና በማኅበረሰቡ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸውንም አስታውቋል፡፡

በሃይማኖት ሽፋን ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር መታወቁንም አመልክቷል፡፡

እነዚህ ጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ ባሕልና ዕሴት እንዲሁም ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባፈነገጠ መንገድ በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ገዳም ውስጥ ምሽግ በመቆፈር ሕዝቡ ቅዱስ የሚለውን ሥፍራ የጦር አውድማ በማድረግ ለማርከስ ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡

ነገር ግን በዋናነት የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በመቀናጀት በወሰዱት ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ሴራው መክሸፉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይሉ አስታውቋል፡፡

በታጣቂዎቹም ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ የተለያዩ ከባድና ቀላል መሣሪያዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁሟል፡፡

200 የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ታጣቂዎች መደምሰሳቸውንና የቀሩትም ከመማረካቸውና ከመሸሻቸው ውጪ ÷ ቡድኑ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በሚነዛባቸው የማኅበራዊ ትሥሥር ገፆች በመንግሥት ጸጥታ አካላት በገዳሙና በምዕመናን ጉዳት እንዳደረሰ ተደርጎ የሚሠራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ እርምጃ በወሰዱበት በዚህ ሕግ የማስከበር ስምሪት የአካባቢው ማኅበረሰብ መረጃ በመስጠትና በሌሎችም መንገዶች ያደረገው ትብብር የሚደነቅ መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ገልጾ ለዚህም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በቀጣይም ክልሉ ከጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች ጸድቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን ለሚደረገው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ የጋራ ጥረቱንና አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.