ኢትዮጵያ በተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መድረክ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት የዓመቱ አጋማሽ የድርድር መድረክ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት በየዓመቱ ሰኔ ወር ላይ የሚካሄድ ሲሆን÷ ስብሰባው በዛሬው ዕለት በጀርመን ቦን ከተማ ተጀምሯል፡፡
የስብሰባው ዋና ዓላማ በቀጣዩ አመት ታህሳስ ወር በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ለሚካሄደው 28ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የሚቀርቡ የውሳኔ ሀሳቦች በአባል ሀገራቱ እንዲቀርፁ ለማድረግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመድረኩ በፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ሲሆን÷ ልዑኩ በአፍሪካ ቡድን፣ በቡድን 77 እና በቻይና ቡድን የዝግጅት ስብሰባዎች ላይ ተሳትፏል፡፡
ዛሬ በሚደረገው ስብሰባም በተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች ዙሪያ በጥልቀት በመወያየት ለ28ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የሚቀርቡ የውሳኔ ሀሳቦች ይዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሳንዶካን ከዚህ ውይይት ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት፣ ቡድኖችና ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን ያደርጋሉ መባሉን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡